12/06/2024
የኦሊምፒክ ኮሚቴው ሚስጥራዊ ጉባኤ...
🔵አስር ወር የሚቀራቸው ዶ/ር አሸብር ለ3ኛ ጊዜ ተመርጠዋል
🔵 ሀይሌ፣ ደራርቱና ብርሀኔ ምክትል ሆነዋል
🔵 በምርጫው የሀገሪቱ ህጎች ተጥሰዋል
ትናንት ሰኔ 4/2016 ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ውስጥ ጥብቅና ሚስጥራዊ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፤ መረጃ እንዳይወጣ ታፍኖ፥ መገናኛ ብዙሀን እንዳይሰሙ ተደርጎ ምርጫ ተከናውኗል፤ ስለ ጉዳዩ ከአንተ መስማታችን ነው ያሉኝ ጋዜጠኞችና ፌዴሬሽኖችም ነበሩ፤ መንግስታዊው የባህልና ስፖርት ሚንስቴር እንኳን በስፍራው አልተገኘም
ነገሮችን በስሌት በመበለት የተካኑት ብቸኛው እጩ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የሀገሪቱ ህግ ባይፈቅድላቸውም ለሶስተኛ ጊዜ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፤ የያዙት ወንበር ገና አስር ወር ቢቀረውም ሌላ የስልጣን ዘመን ሸምተዋል፤ ሌሎች ተመራጮችም አሉ፥ ዝርዝሩን እነሆ፦
★ የምርጫ ቅድመ ዝግጅትና ሚስጥራዊነት
ከአስራ አምስት ቀናት በፊት በማሪዮት ሆቴል ለትናንቱ ጉባኤ ይረዳ ዘንድ የተመረጡ ተሳታፊዎችን የማሳመንና የደንብ ማሻሻያ ውይይት ተካሂዶ ነበር፤ በዋናነት ዶክተሩን ለሶስተኛ የስራ ዘመን ለማስመረጥ የማግባባት ስራ ተከናውኗል፤ ሌሎች ፌዴሬሽኖች ተወዳዳሪ እንዳያቀርቡና ዶ/ር አሸብር ብቸኛ እጩ እንዲሆኑ ከፍተኛ የማሳመን ጫና ተደርጓል፤ በተጨማሪ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቋሚነት የኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታን እንዲይዝ ደንብ ተሻሽሎ ፀድቋል፤ ፌዴሬሽኖች ለአመራርና ለስራ አስፈፃሚነት እጩ መላክ ቢኖርባቸውም አንዳንዶቹ አልደረሰንም ብለዋል፤ በተለምዶ እጩ ለመላክና ለመገምገም የአንድ ወር ጊዜ ቢሰጥም ገሚሱ ምርጫ መኖሩን ሳያውቅ ሌላው ተወካዩን ሳይልክ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ተጣድፎ ምርጫው ተከናውኗል፤ ትናንት የይስሙላ ምርጫ በጉባኤው ተደረገ እንጂ ሁሉም ነገር ያለቀው ከአስራ አምስት ቀናት በፊት ነበር ብለውኛል ምንጮቼ
እናም በትናንቱ ምርጫ ብቸኛው እጩ ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ለሶስተኛ የስራ ዘመን ኦሊምፒክ ኮሚቴን እንዲመሩ ተሹመዋል፤ ከስራቸው ደግሞ ሶስት ምክትሎች ተሰይመዋል፤ ከዚህ በፊትም ምክትል የነበሩት የቀድሞ አትሌቶቹ ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴና ኮማንደር ብርሀኔ አደሬ አሁንም በምክትልነት ፕሬዝዳንትነታቸው ቀጥለዋል፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቋሚነት የኦሊምፒክ ኮሚቴው ምክትል ይሆናል በሚለው አዲሱ ደንብ መሰረት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በምክትል ማዕረግ ተሹማለች፤ አቶ ዳዊት አስፋው በዋና ፀሀፊነት ዶ/ር ኤደን አሸናፊ በአቃቢተ ንዋይነት ልክ እንደቀደመው ሀላፊነታቸው አሁንም ቀጥለዋል
የትናንቱ ምርጫ በሚስጥር የተያዘ ለመገናኛ ብዙሀን ዝግ የሆነ ለብዙዎች ድንገቴ ነበር፤ የመንግስት አካል የሆነው የባህልና ስፖርት ሚንስቴር በሁሉም ምርጫዎች ላይ በታዛቢነት መገኘት ቢኖርበትም በትናንቱ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉባኤ ላይ ግን አልነበረም፤ በተመሳሳይ የኦሊምፒክ ምርጫን ማከናወን ያለባቸው የኦሊምፒክ ስፖርቶች የሆኑ ፌዴሬሽኖች ቢሆኑም አንዳንዶቹ በጉባኤው እንዳልተገኙ ከተሳታፊዎቹ አረጋግጫለሁ፤ ለምሳሌ የትልቁ ተቋም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተወካይ አልተገኘም፤ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ግን ከተቋሙ የተወከለ አባሉን ልኳል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ይፋዊ ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ገልፀውልኛል፤ ስለ ጉባኤው በስልክ የቴሌግራም ግሩፕ መልዕክት የደረሳቸውም ነበሩ፤ ስብሰባው በተደረገበት ቦታ ደግሞ ጥብቅ ቁጥጥርና ጥበቃ ታይቷል፤ ምናልባት ባለፈው ምርጫ እንዳጋጠመው ወከባና የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይኖር በመስጋት ሊሆን ይችላል ተብሏል
★ ጊዜውን ያልጠበቀው ምርጫ
ዶ/ር አሸብርና የቦርድ አባላቱ የስራ ዘመናቸው ገና አልተጠናቀቀም፤ በአወዛጋቢ ሁኔታ የተመረጡት መጋቢት 20/2013 ነበር፤ የአራት አመት የስልጣን ጊዜያቸው ሊያበቃ ገና አስር ወር ይቀረዋል፤ ለምን ታድያ አሁን የሚለው መልስ የሚፈልግ ጥያቄ ነው፤ ይህ መሰል ክስተት ግን የመጀመሪያ አይደለም፤ ከሶስት አመት በፊት አወዛጋቢ የነበረው ምርጫ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ መስከረም ላይ እንዲደረግ በጉባኤው ቢወሰንም ፕሬዝዳንቱ ከኦሊምፒኩ በፊት መጋቢት ላይ ምርጫ አካሂደው በድራማዊ ትዕይንት ስልጣናቸውን ማስቀጠላቸው ይታወሳል፤ ያኔ ቅድሚያ ባህርዳር ሲከለከሉ ወደ ሀዋሳ ሄደው ሀዋሳም በፀጥታ ሀይሎች ተሳደው አዲስ አበባ በኮሚቴው ፅህፈት ቤት በር ዘግተው ምርጫ ማከናወናቸውና 13 ማህበራት መቃወማቸው ብሎም ፕሬዝዳንቱ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፤ አሁን ደግሞ በፓሪስ ኦሊምፒክ ዋዜማ ላይ በድንገቴ ምርጫ ዙፋናቸውን አስቀጥለዋል
★ ቤተኛ ተመራጮችና ጥያቄ የሚያስነሱ አባላት
ስልጣኑን ባላጠናቀቀው የኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራር ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ አመራሮችና የቦርድ አባላት በድጋሚ ለቀጣዩ አራት አመታት ኦሊምፒክ ኮሚቴውን እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፤ ከሀያዎቹ የቦርድ አባላት መካከል አስራ አራቱ ነባር ቤተኛ ናቸው፤ ከነባሮቹ መካከል አሁንም በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲቀጥል የተሾመው ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ በኦሊምፒክ ኮሚቴው እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ አድርጎ አያውቅም፤ በስብሰባዎችና በጉባኤ ላይም አይገኝም፤ አሁንም ግን ድጋሚ ተመርጧል፤ አዲስ ከገቡት መካከልም ጥያቄ የሚነሳባቸው አባላትና ማህበራት አሉ፤ ለምሳሌ የኦሊምፒክ ስፖርት ያልሆነው የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የኦሊምፒክ ኮሚቴ የቦርድ አባል ሆኖ መካተቱ አስገራሚ ሆኗል፤ በሌላ በኩል ከኦሊምፒክ እኩል አቻ የሆነው ፓራ ኦሊምፒክ በተመሳሳይ መካተቱ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፤ አራት አትሌቶች፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ፓራ ኦሊምፒክ፣ ክልሎችና የአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ተወካይ ያለ ምርጫ በቀጥታ የቦርድ አባላት ሆነዋል
★ የተጣሱት የሀገሪቱ ህጎች
አንድ፦ የሀገሪቱ የስፖርት ማህበራት ህግ እንደሚለው አንድ ስራ አስፈፃሚ ለሁለት የስራ ዘመን ወይም ለስምንት አመት ብቻ ማገልገል አለበት፤ ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደርም መመረጥም አይችልም፤ በአጭሩ የስልጣን ዘመኑ ስምንት አመት ብቻ ነው፤ ይህ ህግ ለሁሉም የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ማህበራት የሚውል ነው። የኦሊምፒክ ኮሚቴው አለቃ ግን ይህንን ህግ ጥሰው ለሶስተኛ የስራ ዘመን ትናንት በሚስጥር ተመርጠዋል፤ የገዢው ፓርቲና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር አሸብር እኛ የአለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ህግ እንጂ የሀገሪቱ መንግስት የሚያወጣው ህግ አይገዛንም የሚል አቋም ይዘው ግዙፉን ተቋም እስከ አስራ ሁለተኛ አመታቸው ለመምራት ተዘጋጅተዋል፤ በዚህም ህጉን ሽረው ተሹመው ሌሎቹን ሹመዋል፤ ይህ ክስተት በሌሎች ፌዴሬሽኖች ላይም እንዳይዛመት ያስፈራል፤ በሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ላይ የሚገኙት የእግርኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች ለሶስተኛ ዙር ምርጫ ሊወዳደሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ፤ ስለሆነም ህጉን ማስከበር አልያም ማሻሻል ተገቢ ነው
ሁለት፦ የክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና የፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ሀላፊዎች በማህበራት ጉባኤዎች ላይ መመረጥና በድምፅ መሳተፍ እንደማይችሉ ገለልተኛ ሆነው ብቻ እንዲሳተፉ የስፖርት ማህበራት ህጉ ይደነግጋል፤ አሁን ግን የክልል ኦሊምፒክ ቅርንጫፎች በሚል በቦርድ አባልነት ገብተዋል፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዲሁም የሀረሪና የአማራ ስፖርት ኮሚሽኖች የኦሊምፒክ ኮሚቴ የቦርድ አባል ሆነው ተመርጠዋል፤ መንግስታዊ ተቋማትን በማስገባት ይህም ህግ ተሽሯል
ሶስት፦ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው በማህበራት አመራርነት መመረጥ እንደማይችሉ በዚሁ የስፖርት ማህበራት ህግ ላይ ተቀምጧል፤ ሁለቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊው አቶ ዳዊት አስፋው በዋና ፀሀፊነት እንግሊዛዊቷ ዶ/ር ኤደን አሸናፊ ደግሞ በአቃቢተ ነዋይነት በድጋሚ ተመርጠው ህጉ ፋይዳ እንደሌለው አሳይተዋል
አራት፦ የኦሊምፒክ ስፖርት ያልሆኑ ማህበራት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ድምፅ ሰጪ ተመራጭ አባል ወይም መሪ ሆነው መስራት እንደማይችሉ ሀገራዊው ህግ ያዛል፤ ትናንት ግን ከኦሊምፒክ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የባህል ስፖርቶች ተመርጧል
★ እነማን ተመረጡ?
አንድ ፕሬዝዳንት፣ ሶስት ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ አንድ ዋና ፀሀፊ፣ አንድ አቃቢተ ንዋይ፣ 13 የቦርድ አባላት፣ አራት አትሌቶች፣ ሁለት ፌዴሬሽኖችና ሁለት ክልሎች በትናንቱ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉባኤ ተሰይመዋል፤ በተጨማሪ በአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ በከፍተኛ ሀላፊነት ላይ የሚገኙት ወ/ሮ ዳግማዊት ፀሀዬ በድጋሚ ተካተዋል፤ እንደ ሀይሌ ሁሉ ወ/ሮ ዳግማዊትም በዶ/ር አሸብር ካቢኔ ውስጥ ብዙም ተሳትፎ የሌላቸው እንደውም በግፍ የተገፉ ሙያተኛ ናቸው
ሙሉ ተመራጮቹን እነሆ፦
1 ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ.. ከቅርጫት ኳስ... ፕሬዝዳንት.
2 ረዳትኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ..ከአትሌቲክስ..ምክትል ፕሬዝዳንት
3 ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ...አትሌት...ምክትል ፕሬዝዳንት
4 ኮማንደር ብርሀኔ አደሬ...አትሌት...ምክትል ፕሬዝዳንት
5 አቶ ዳዊት አስፋው...ከቴኳንዶ...ዋና ፀሀፊ
6 ዶ/ር ኤደን አሸናፊ... ከብስክሌት...አቃቢተ ንዋይ
7 ዶ/ር ግዮን ሰይፉ...ከፓራ ኦሊምፒክ...የቦርድ አባል
8 ዶ/ር ፍትህ ወልደሰንበት...ከእጅ ኳስ...የቦርድ አባል
9 አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ...ከካራቴ...የቦርድ አባል
10 አቶ መስፍን አበራ...ከቮሊቦል...የቦርድ አባል
11 አቶ ጥላሁን ታደሰ... ከክብደት ማንሳት...የቦርድ አባል
12 አቶ ሲሳይ ዮሀንስ...ከጠረጴዛ ቴኒስ...የቦርድ አባል
13 ወ/ሮ ህይወት መሀመድ..ከባህል ስፖርት..የቦርድ አባል
14 አቶ ሚንልክ ሀብቱ...ከቦውሊንግ...የቦርድ አባል
15 አትሌት ቀነኒሳ በቀለ....አትሌት...የቦርድ አባል
16 አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ...አትሌት...የቦርድ አባል
17 አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር....የቦርድ አባል
18 ሀረሪ ክልል...የቦርድ አባል
19 አቶ ባዘዘው ጫኔ...ከአማራ...የቦርድ አባል
20 ወ/ሮ ዳግማዊት ፀሀዬ...ከአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ...የቦርድ አባል ሆነዋል
★ ጥያቄዎች?
የትናንቱ ጉባኤ ለምን በዝግና በሚስጥር ተካሄደ? አንዱን ፌዴሬሽን በመጥራት ሌላውን በመዝለል ለምን ተከናወነ? የምርጫው ጊዜ ሳይደርስ ለምን ምርጫ ተካሄደ? ከአንድም አራት የስፖርት ማህበራት ህጎች ሲሻሩ ለምን ዝምታን ተመረጠ? እግርኳስ ፌዴሬሽን ለምን ተወካይ አላከም? ለምን የቦርድ አባልነት ውስጥ አልገባም? ከሶስት አመት በፊት ምርጫ ሲካሄድ ህገወጥ ነው ብሎ ሰልፍ የወጣው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ተመሳሳይ ነገር ሲፈፀም ለምን ዝምታን መረጠ? ባህልና ስፖርት ሚንስቴርስ ለምን ጉዳዩን ችላ አለው? እኮ ለምን?
via(ታምሩ ዓለሙ)
11/06/2023
በሊጉ ለመቆየት ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን ወልቂጤ ከተማን ወንድ ሴት፤ ህፃን አዛውንት ሳይቀር በእስታድም እየተገኙ የክለቡ ደጋፊዎች የተለመደ ድጋፋቸውን እየሰጡት ነው።
እንዳለመታደል ሆኖ ዛሬም ክትፎዎቹ ከመቻል ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 2ለ0 ቢሸነፉም የደጋፊዎቹ ስሜት ግን ቀልብን ስቧል።
እግር ኳስ ❤️
11/06/2023
በበጀት ዓመቱ ከምንጊዜውም የተሻለ አፈፃፀም የታየበት እና ውጤት ያስመዘገበበት ዓመት እንደነበር የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
ሰኔ 03/2015ዓ.ም
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን የጉባኤ አባላትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ በጉባኤ መክፈቻ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከምንጊዜውም የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት እና ስፖርቱን ለማሳደግ አበረታች እንቅስቃሴ የተደረገበት እንደነበር አስታውቀዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና በስኬት ከመጠናቀቁ ባሻገር ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር ገልፀዋል።
በሻምፒዮናው ዳኞች ባሳዩት ብቃት ለመጀመሪያ ጊዜ በአህጉር አቀፍ ደረጃ እንዲዳኙ እድል ያገኙበት ዓመት ነበር ብለዋል።
በቀጣይ የ2024 የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና አስተናጋጅነት ዕድል ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ይሁንና ስፖርቱን ለማሳደግ እና በአህጉር እና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በስፋት ለመሳተፍ የበጀት እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።
ጉባኤው የ19ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ-ጉባኤ እና የ2014ዓ.ም የኦዲት ሪፖርት መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በተጨማሪም የ2014 - 2015ዓ.ም የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በሪፖርቱ ለአሠልጣኞች እና ዳኞች አለም አቀፍ ስልጠናዎች እንዲሰጡ መደረጉ እንዲሁም በታዳጊዎች እና ወጣቶች ዙሪያ በመስራት የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት ለክልሎች የስልጠና ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል።
የአሠልጣኞች እና ተጨዋቾች ከክለብ ክለብ ዝውውር ህጋዊ አሠራር እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የጉባኤው አባላትም የቀረበውን ሪፖርት አድንቀው ፤ ቢስተካከሉ እና ቢጨመሩ ያሏቸውን ሀሳብ እና አስተያየት ስጥተዋል።
በመጨረሻም ጉባኤው ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ለተቋማዊ ግንኙነት የሚጠቀምበትን አርማ (ሎጎ) በማፅደቅ ተጠናቋል።
09/06/2023
2ኛው ዙር የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠ/ቴኒስ ክለብ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
ሰኔ 02/2015 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከግንቦት 29 - ሰኔ 02 /2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ የቆየው 2ኛው ዙር የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በውድድሩ በታዳጊ ወንዶች የነጠላ ውድድር ፦
ዳንኤል ወርቁ እና ዳንኤል ታደሰ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ኛና 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ ፤ ዳግማዊ ተስፋዬ ከኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ 2ኛ ሆኗል ።
በተመሳሳይ በታዳጊ ሴቶች የነጠላ ውድድር፦
ይርጋለም ያለው እና ኤደን ይፍጠር ሁለቱም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ኛና 3ኛ ደረጃን ሲይዙ ፤ ፍሬህይወት ጊዲና ከኦሮሚያ ፖሊስ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች ።
በአዋቂ ወንዶች የነጠላ ውድድር፦
አማኑኤል አመሃ እና ኤደን ተስፋዬ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ኛና 3ኛ ሲሆኑ ደራራ መኮንን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ኛ ሆኗል ።
በአዋቂ ሴቶች የነጠላ ውድድር ፦
ማርታ መሸሻ ፣ ሜሮን ጌታነህ እና ፍትሐዊት ግደይ በቅደም ተከተል ሁሉም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1ኛ -3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን ጨርሰዋል ።
በሌላ በኩል በታዳጊ ወንዶች የቡድን ውድድር ፦
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኦሮሚያ ፖሊስ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል ።
በታዳጊ ሴቶች የቡድን ውድድር፦
ኦሮሚያ ፖሊስ 1ኛ ሲሆን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ኛ እንዲሁም የኔነህ አዲስ ስፖርት ክለብ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል ።
በአዋቂ የቡድን ውድድር፦
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለቱም ፆታ አንደኛ በመሆን ሲያጠናቅቅ ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ እንዲሁም ኦሮሚያ ፖሊስ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን ጨርሰዋል ።
በውድድሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠረጴዛ ቴኒስ ክለብ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል ።
ለ4 ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ውድድር ከስድስት ክለቦች የተውጣጡ ከ90 በላይ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል ።
09/06/2023
ለሁሉም የስፖርት ሚዲያዎች
የሚዲያ ሽፋን ጥያቄን ይመለከታል
የአፍሪካ ዞን 4 የጎልፍ ስፖርት ሻምፒዮና ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከግንቦት 28/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እየተካሄደ እንደሆነ ይታወቃል ።
በመሆኑም የወድድሩ መዝጊያ ነገ ቅዳሜ ሰኔ 03 /2015 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጀምሮ ጦር ኃይሎች በሚገኘው ጎልፍ ክለብ በመሆኑ በዕለቱና በሰዓቱ በቦታው በመገኘት መረጃውን ለህዝብ እንድታደረሱ የኢትዮጵያ ጎልፍ አሶሴሽን ጥሪውን ያስተላልፋል ።
08/06/2023
በሴቶች ጥሎ ማለፍ የቮሊቦል ውድድር ጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብ ሻምፒዮን ሆነ ።
****===****===****===****===****====****
ሰኔ 01/2015 ዓ.ም
በሴቶች ጥሎ ማለፍ የቮሊቦል ውድድር ጌታ ዘሩ ስፖርት ክለብ ብሄራዊ አልኮልን በማሸነፍ ሻምፒዮን መሆን ችሏል።
ዛሬ ፍፃሜውን ባገፕው የ2015 ዓ.ም የሴት ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር ለ3ኛ ደረጃ በተካሄደ ጨዋታ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን 3-0 ሲያሸንፍ በፍፃሜው ጌታ ዘሩ ብሄራዊ አልኮልን 3-1 በማሸነፍ የ2015 ዓ.ም ሻምፒዮን ሆኗል።
06/06/2023
የአፍሪካ ዞን 4 የጎልፍ ስፖርት ሻምፒዮና ውድድር የመክፈቻ ፕሮግራም ጦር ኃይሎች በሚገኘው ጎልፍ ክለብ በደማቅ ሆኔታ እየተካሄደ ይገኛል ።
በመክፈቻ ፕሮግራሙ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የጎልፍ ስፖርት ቤተሰቦቾ ተገኝተዋል ።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከግንቦት 29 - ሰኔ 04/2015 ዓ.ም በሚካሄደው የአፍሪካ ዞን 4 የጎልፍ ስፖርት ሻምፒዮና ውድድር እስካሁን አምስት ሀገራት በውድድሩ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል ።
05/06/2023
ለሁሉም የስፖርት ሚዲያዎች
የሚዲያ ሽፋን ጥያቄን ይመለከታል
የአፍሪካ ዞን 4 የጎልፍ ስፖርት ሻምፒዮና ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከግንቦት 28 - ሰኔ 04/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል ።
በመሆኑም የወድድሩ መክፈቻ ነገ ማክሰኞ ግንቦት 29/2015 ዓ.ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጦር ኃይሎች በሚገኘው ጎልፍ ክለብ በመሆኑ በዕለቱና በሰዓቱ በቦታው በመገኘት መረጃውን ለህዝብ እንድታደረሱ የኢትዮጵያ ጎልፍ አሶሴሽን ጥሪውን ያስተላልፋል ።
04/06/2023
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አመታዊ ማጠቃለያ ውድድር ትናንት ተጀምሯል ።
ግንቦት 27/2015 ዓ.ም
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕርሚየር ሊግ ውድድር ከ15ኛ እስከ 18ኛ ሳምንት አመታዊ ማጠቃለያ ውድድር ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ትንሿ ስቴዲየም በደማቅ ሁኔታ ተጀምሯል ።
ውድድሩ እስከ ሰኔ 03/2015 የሚካሄድ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ፌደራል ማረሚያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና መቻል ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የውጤት ባለቤት ሁነዋል።
የ15ኛ ሳምንት ውድድር ውጤት 26/9/2015 ቅዳሜ
1. ከምባታ ዱራሜ Vs ፌደራል ማረሚያ 31 ለ 32 አሸናፊ ፌደራል ማረሚያ
2. ፋሲል ከነማ Vs ቂርቆስ ክፋለ ከተማ 18 ለ 42 አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ
3. መቻል Vs ኦሜድላ 47 ለ 42 አሸናፊ መቻል።
ውድድሩ ነገ ሰኞ ግንቦት 28/2015 የሚቀጥል ሲሆን
3:00 — ፋሲል ከነማ Vs ፌደራል ማረሚያ
4:30 — መቻል Vs ባህርዳር ከነማ
ውድድራቸውን እንደሚያደርጉ የወጣው ፕሮግራም ያመላክታል ።
31/05/2023
7ኛው የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ተጀመረ ።
ግንቦት 23/2015 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ያዘጋጀው 7ኛው የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ዓመታዊ ሻምፒዮና ውድድር በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል ።
ውድድሩ በሁለቱም ፆታ የሚካሄድ ሲሆን ከሲዳማ ፣ ከኦሮሚያ ፣ ከአማራ ፣ ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ የተውጣጡ ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል ።
ትናንት በመክፈቻው በተደረገ የሴቶች ውድድር ፦
አማራ ሲዳማን 22 ለ 7 ፤ አዲስ አበባ ድሬዳዋን 43 ለ 0 ሲያሸንፋ ፤
በወንዶች በተደረገ ውድድር ፦
አመራ ሲዳማን 54 ለ 2 እንዲሁም አዲስ አበባ ድሬዳዋን 61 ለ 13 ማሸነፍ ችሏል ።
በተመሳሳይ ዛሬ በተደረገ የሴቶች ውድድር ፦
ሲዳማ ድሬዳዋን 41 ለ 2 ፤ አማራ ኦሮሚያን 29 ለ 24 በሆነ ውጤት ሲያሸንፋ ፤
በወንዶች ድሬዳዋ ሲዳማን 17 ለ 2 ፤ አማራ ኦሮሚያን 23 ለ 21 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል ።
ውድድሩ ነገም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን ግንቦት 27/2015 ዓ.ም ፍፃሜውን የሚያገኝ ይሆናል ።
ውድድሩ አካል ጉዳተኞች በስፖርት ያላቸውን ተሳትፎ ለማጎልበትና ከተወዳዳሪዎቹ የተሻለ ብቃት ያላቸውን በመምረጥ ለአህጉር አቀፍ ውድድሮች ለማዘጋጀት መሆኑን አሶሴሽኑ አስታውቋል ።
16/05/2023
በዓለም የቦክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ቦክስ ብሔራዊ ቡድን አቀባበል ተደረገለት ።
ግንቦት 08/2015 ዓ.ም
በኡዝበኪስታን ታሽካንት ከተማ ከሚያዝያ 22 - ግንቦት 7/2015 ዓ.ም በተካሄደው የዓለም የወንዶች ቦክስ ሻምፒዮና ውድድር የተሳተፈው የኢትዮጵያ ቦክስ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት አቀባበል ተደርጎለታል ።
ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ሌሊት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን በዛሬው ዕለት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይ ፣ የፌዴረሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላት ፣ የክለብ አመራሮች እና አሠልጣኞች በተገኙበት በኢትዮጵያ ሆቴል አቀባበል የተደረገለት ።
በአቀባበሉ ላይ የተገኙት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የውድድር ዴስክ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳርጌ እንዳሉት ብሔራዊ ቡድኑ በአደረገው ውድድር ጥሩ ተፎካካሪ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ፤ በቀጣይ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመተባበር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንሰራለን ብለዋል ።
በተለይ በቀጣይ ዓመት የፓሪስ ኦሎምፒክን ጨምሮ የተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሄድበት በመሆኑ ሀገራችን ውጤታማ ሊያደርጉ በሚችሉ ስፖርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል ።
ለዚህ ዝግጅት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ቦክስን ጨምሮ አትሌቲክስ ፣ እግርኳስ ፣ ብስክሌት እና ቴኳንዶ ስፖርቶችን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የጥናት ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል ።
የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ም/ፕረዚዳንት አቶ አብዱልሰመድ መሀመድ በበኩላቸው ተወዳዳሪዎች ፈታኝ ሆኔታዎችን በማለፍ በውድድሩ መሳተፋቸውን ገልፀው ፤ በቀጣይ ከዚህ በመማር ለተሻለ ውጤት እንሰራለን ብለዋል ።
በውድድሩም ከፍተኛ ልምድ የተገኘበት መሆኑን ገልፀዋል ።
በውድድሩ ከ127 ሀገራት የተውጣጡ ቦክሰኞች የተሳተፋ ሲሆን ኢትዮጵያ በ3 ኪሎ ካታጎሪ በ51ኪ.ግ ዳዊት በቀለ ፣ በ63.5 ኪ.ግ መስፍን ብሩ እና በ67 ኪ.ግ ቢኒያም አበበ ተወክላለች ።
በ51ኪ.ግ ኢትዮጵያን የወከለው ዳዊት በቀለ የቡሩንዲ አቻውን በከፍተኛ የነጥብ የበላይነት ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ፤ ሁለተኛ ጨዋታውን ከታይዋን አቻው ጋር አድርጎ ሊሸነፍ ችሏል ።
በሌላ በኩል በ63.5 ኪ.ግ የተሳተፈው መስፍን ብሩ የሳይፕረስ አቻውን በማሸነፍ በኩባ አቻው ተሸንፏል ።
በ67 ኪ.ግ ኢትዮጵያን የወከለው ቢኒያም አበበ በራሺያ አቻው ጋር ብርቱ ፋክክር በማድረግ ተሸንፏል ።
13/02/2023
ዜና ዕረፍት
ሲኒየር ዓለም አቀፍ የቮሊቦል ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
===****====፣****===****፣===****====
በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ ለረጅም ዓመታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ በተለይ
✅ የስፖርት ፖሊሲ እንዲወጣ ከፍተኛ ሀላፊነት የወሰደ፣ በተለያዩ ሀላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገለ፣
✅ በቮሊቦል ሲኒየር ዓለም አቀፍ የቮሊቦል ኢንስትራክተር በመሆን ለረጅም ዓመታት ከ150 በላይ የዓለም ሀገራት በመሄድ ስልጠናዎችን በመስጠት ሀገሩን በዓለም አቀፍ መድረክ ያስጠራ
✅ የኢትዮጵያ ቮሊቦል አባት ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ሲኒየር ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ዓለማየሁ ሸዋታጠቅ ባለትዳርና የአንድ ወንድ እና የአንድ ሴት ልጅ አባት የነበረ ሲሆን የቀብር ስነ ስርዓቱም በ7/6/2015 ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ በካቴድራል ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቹ ፣ከፍተኛ የስፖርት አመራሮች፣የሙያ ልጆቹና የስፖርት ቤተሰቡ በተገኙበት ይፈፀማል።
በእንጋፋውና እውቁ ባለሙያ ህልፈተ ህይወት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀን፤ለቤተሰቡ፣ወዳጅ ዘመዱና ለስፖርት ቤተሰቡ መጽናናትን እንመኛለን ።