27/03/2020
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው
*******************
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው ተረጋገጠ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀለል ያሉ የቫይረሱ ምልክቶች የታየባቸው ሲሆን እራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩም ቢቢሲ ዘግቧል።
27/03/2020
ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የሚወክሉ 15 አዳዲስ አምባሳደሮች ምደባ ይፋ ሆነ
******************
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የሚወክሉ 15 አዳዲስ አምባሳደሮች ምደባ ዛሬ ይፋ ሆነ።
በዚህም መሠረት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮች:-
1. አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ-አውስትራሊያ፣ ካንቤራ
2. አምባሳደር ያለም ፀጋይ- ኩባ ሃቫና
3. አምባሳደር ሂሩት ዘመነ- ቤልጄም፣ ብራሰልስ
4. አምባሳደር ዶ/ር ማርቆስ ተክሌ-ግብጽ፣ ካይሮ
5. አምባሳደር ባጫ ጊና ሞሮኮ፣ራባት
6. አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ- ሱዳን፣ ካርቱም
7. አምባሳደር ምሕረተአብ ሙሉጌታ-ኤርትራ፣ አስመራ
8. አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው-አልጀሪያ፣ አልጀርስ
9. አምባሳደር ተፈሪ መለስ-እንግሊዝ፣ ለንደን ሆነው እንዲሠሩ ተመድበዋል።
የአምባሳደሮች ምደባን በተመለከተ:-
1. አምባሳደር አድጎ አምሳያ-ስዊድን፣ ስቶክሆልም ምክትል ሚሲዮን መሪ
2. አምባሳደር ጀማል በከር-ባህሬን፣ ማናማ ቆንስል ጄኔራል
3. አምባሳደር አብዱ ያሲን-ሳዑዲ አረቢያ፣ ጄዳ ቆንስል ጄኔራል
4. አምባሳደር ለገሠ ገረመው-ካናዳ፣ኦታዋ ምክትል ሚሲዮን መሪ
5. አምባሳደር ኢየሩሳሌም አምደማርያም-የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች፣ዱባይ ቆንስል ጄኔራል
6. አምባሳደር ሽብሩ ማሞ-አሜሪካ፣ ሚኒሶታ ቆንስል ጄኔራል ሆነው እንዲሠሩ ተመድበዋል።
አምባሳደሮቹ በተመደቡባቸው አገራት የፕሮቶኮል አሠራር መሠረት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቆ በቅርቡ ወደ ምድብ ቦታቸው ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን በይፋ የሚጀምሩ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
27/03/2020
የቡድን 20 አባል ሀገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተዳከመውን የዓለም ኢኮኖሚ ለመደገፍ 5 ትሪሊዮን ዶላር ፈስስ ለማድረግ ቃል ገቡ
*******************
የወቅቱ የቡድን 20 አባል ሀገራት ሊቀመንበር ሳውዲ አረቢያ ያዘጋጀችው የአባል ሀገራቱ የቪዲዮ ኮንፈረንስ የተጠናቀቀ ሲሆን ያንን ተከትሎም አባል ሀገራቱ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
አባል ሀገራቱ በመግለጫቸው ኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የፋይናንስ ጉዳት ለመቋቋም 5 ትሪሊዮን ዶላር ወደ ዓለም ገበያ ፈሰስ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
አባል ሀገራቱ ከዓለም የገንዝብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ ከዓለም የጤና ድርጅት እና ከአህጉራዊ ባንኮች ጋር ሆነው የፋይናንስ ማዕቀፍ በማዘጋጀት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ለመደገፍ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የቡድን 20 አባል ሀገራቱ በጋራ መግለጫቸው በአንድነት በመሆን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመግታት እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
ችግሩን ለመከላከል የተቀናጀ ዓለም አቀፋዊ ምላሽ እንደሚያስፈልግም አስምረውበታል።