16/07/2026
የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ ብሔራዊ ቡድኖች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
የዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ተፋላሚ ብሔራዊ ቡድኖችን የለየ ሲሆን ÷ በዚህም ስፔን እና አርጀንቲና ለዋንጫው ይፋለማሉ፡፡
ስፔን ለዋንጫ የተገመተችውን ሌላኛዋን ሀገር ፈረንሳይን በግማሽ ፍጻሜው 2 ለ 0 በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኗ ይታወሳል፡፡
በአሰልጣኝ ሉዊስ ዴላፎንቴ የምትመራው ስፔን እስካሁን ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቿ ላይ 13 ግቦችን አስቆጥራለች፤ የተቆጠረባት ደግሞ አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡
ስፔን በፈረንጆቹ 2010 የዓለም ዋንጫን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳካች ሲሆን÷ በድጋሚ በመድረኩ ለመንገስ በፍጻሜው ከአርጀንቲና ጋር ትፋለማለች፡፡
ተጋጣሚዋ ሀገር አርጀንቲና ደግሞ በግማሽ ፍጻሜው እንግሊዝን 2 ለ 1 በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ ሆናለች፡፡
በጨዋታው እንግሊዝ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ብትሆንም አርጀንቲና ከመመራት ተነስታ በማሸነፍ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫ መድረክ ፍጻሜ ላይ ተገኝታለች፡፡
አርጀንቲና እስካሁን ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቿ ላይ 19 ግቦችን ያስቆጠረች ሲሆን÷ 7 ግቦችን ደግሞ አስተናግዳለች፡፡
በ2022 የዓለም ዋንጫን ያሳካችው አርጀንቲና በተከታታይ ዋንጫውን ለማሳካት የምታደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
ስፔን በታሪኳ ለ2ኛ ጊዜ እንዲሁም አርጀንቲና ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ለማሳካት የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
የ2026 የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የፊታችን እሑድ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ይደረጋል፡፡
በፍጻሜ ተፋላሚዎቹ ተሸንፈው ጉዟቸው የተገታው እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ደግሞ ለደረጃ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡
በወንድማገኘ ጸጋዬ
15/07/2026
አርጀንቲና እንግሊዝን በማሸነፍ ወደ ፍጻሜ አለፈች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ዋንጫው የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር አርጀንቲና እንግሊዝን በማሸነፍ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
እንግሊዝ በአንቶኒ ጎርደን ግብ እስከ 85ኛው ደቂቃ ድረስ 1 ለ ዐ እየመራች ብትቆይም አርጀንቲና በኢንዞ ፈርናንዴዝ እና ላውታሮ ማርቲኔዝ ግቦች ጨዋታውን አሸንፋለች።
ሊዮኔል ሜሲ ለሁለቱም ግቦች ኳስ አመቻችቶ በማቀበል ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።
አርጀንቲና በፍጻሜው ከስፔን ጋር ትፋለማለች፡፡
15/07/2026
የተጠባቂው ጨዋታ አሰላለፍ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2026 የዓለም ዋንጫ ዛሬ ምሽት አርጀንቲና ከእንግሊዝ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
የተጠባቂው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሰላለፍ ይፋ ሆኗል፡፡
በዚህም መሰረት በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጆርዳን ፒክፎርድ፣ ማርክ ጉኤሂ፣ ጆን ስቶንስ፣ ስፔንስ፣ አንደርሰን፣ ዴክላን ራይስ፣ ሪስ ጀምስ፣ ጁድ ቤሊንግሃም፣ ሞርጋን ሮጀርስ፣ ጎርደን እና ሃሪ ኬን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካትተዋል፡፡
በአርጀንቲና በኩል ደግሞ ኤሚ ማርቲኔዝ፣ ታግላፊኮ፣ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ፣ ክርስቲያን ሮሜሮ፣ ሞሊና፣ ማካሊስተር፣ ኤንዞ ፈርናንዴዝ፣ ፓራዴዝ፣ ስሞን፣ ሊዮኔል ሜሲን እና ጁሊያን አልቫሬዝን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካትታለች፡፡
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ መደረግ የሚጀምር ሲሆን፤ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሸናፊ በፍጻሜው ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር በመጪው እሁድ ዋንጫውን ለማንሳት ይጫወታል፡፡
15/07/2026
አርጀንቲና ከእንግሊዝ - ወደ ፍጻሜው ለማለፍ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የ2026 የዓለም ዋንጫ ውድድር የዋንጫውን ባለቤት የሚወስኑ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ቀርተውታል።
ዛሬ ምሽት በሚደረግ ጨዋታ የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ሌላኛው የፍጻሜ ተፋላሚ ብሔራዊ ቡድን የሚለይ ይሆናል፡፡
በዚህም ምሽት 4 ሰዓት ላይ አርጀንቲና ከእንግሊዝ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
አርጀንቲና ሻምፒዮን በሆነችበት የ1986 የዓለም ዋንጫ "የእግዜር እጅ" በመባል የምትታወቀውና ዲያጎ ማራዶና በእንግሊዝ ላይ በእጅ ያስቆጠራት ግብ ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ሲገናኙ ሁሌም የሚታወስ ታሪክ ነው፡፡
የ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ሀገር አርጀንቲና በተከታታይ በመድረኩ ሻምፒዮን ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ትፋለማለች፡፡
አርጀንቲና በምድብ ጨዋታዎች ከአልጄሪያ፣ ኦስትሪያ እና ጆርዳን እንዲሁም በጥሎ ማለፍ ከኬፕ ቨርዴ እና ግብጽ ጋር የተገናኘች ሲሆን፥ በሩብ ፍጻሜው ስዊዘርላንድን አሸንፋ ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀሏ ይታወሳል፡፡
የስምንት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ምርጥ ብቃቱን በየጨዋታው እያሳየ ይገኛል፡፡
ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ግማሽ ፍጻሜ ላይ መገኘት የ39 ዓመቱ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ሚና የሚተካ አይደለም፡፡
ሜሲ በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ እስካሁን ድረስ ባደረጋቸው ጨዋታዎች 8 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
በፈረንጆቹ 1966 የዓለም ዋንጫን ካሸነፈች በኋላ ለ60 ዓመታት ያህል ዋንጫውን ማሳካት ያልቻለችው እንግሊዝ ከዘመናት ጥበቃ በኋላ ሻምፒዮን ለመሆን ተቃርባለች፡፡
እንግሊዝ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር ከክሮሺያ፣ ጋና፣ ፓናማ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ሜክሲኮ እና ኖርዌይ ጋር መገናኘቷ ይታወሳል፡፡
በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በኩል አምበሉ ሃሪ ኬን እና ጁድ ቤሊንግሃም በዓለም ዋንጫው አስደናቂ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
ሁለቱም ተጫዋቾች በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ እስካሁን ድረስ በተመሳሳይ ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡
የዘመናትን የዓለም ዋንጫ ጥያቄዋን ለመመለስ በ2018 ተቃርባ የነበረችው እንግሊዝ በግማሽ ፍጻሜው በክሮሺያ ተሸንፋ ውጥኗ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡
ተጠባቂውን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አሜሪካዊው ዳኛ ኢስማኤል ኤልፋት በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል፡፡
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሸናፊ በፍጻሜው ከስፔን ጋር ለዋንጫው የፊታችን እሁድ ይጫወታል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
14/07/2026
ስፔን ፈረንሳይን በማሸነፍ ወደ ፍጻሜ አለፈች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ዋንጫው የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ስፔን ፈረንሳይን በማሸነፍ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
የስፔንን ግቦች ኦያርዛባል (በፍጹም ቅጣት ምት) እና ፔድሮ ፖሮ አስቆጥረዋል።
ስፔን በፍጻሜው ከእንግሊዝ እና አርጀንቲና አሸናፊ ጋር ትገናኛለች፡፡
14/07/2026
ማንቼስተር ዩናይትድ ዩሪ ቴሊማንስን አስፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ ቤልጂየማዊውን የመሐል ሜዳ ተጫዋች ዩሪ ቴሊማንስን ከአስቶን ቪላ ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ ለዝውውሩ 35 ሚሊየን ፓውንድ የውል ማፍረሻ በመክፈል ተጫዋቹን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡
የ29 ዓመቱ አማካይ በኦልድትራፎርድ እስከ ፈረንጆቹ 2031 ድረስ የሚያቆውን ውል ፈርሟል፡፡
ቴሊማንስ በ2023 ከሌስተር ሲቲ አስቶን ቪላን የተቀላቀለ ሲሆን፥ በተጠናቀቀው የ2025/26 የውድድር ዓመት ከቪላ ጋር የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ማሳካቱ ይታወሳል፡፡
ተጫዋቹ በዚህ ክረምት ለማንቼስተር ዩናይትድ ፊርማውን ያኖረ ሦስተኛው ተጫዋች ሲሆን፥ ዩናይትድ ቀደም ሲል ሌላኛውን አማካይ አንድሬይ ሳንቶስ ከቼልሲ እንዲሁም ዌልሳዊውን ግብ ጠባቂ ካርል ዳርሎን በነጻ ዝውውር ማስፈረሙ ይታወቃል፡፡
14/07/2026
ስፔን ከፈረንሳይ - የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቋሚ አሰላለፍ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2026 የዓለም ዋንጫ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ፈረንሳይ ከስፔን የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በምሽቱ ጨዋታ የሚጠቀሙትን ቋሚ አሰላለፍ ይፋ አድርገዋል፡፡
በዚህም መሰረት ስፔን ኡናይ ሲሞን፣ ፔድሮ ፖሮ፣ ኩባርሲ፣ ላፖርት፣ ኩኩሬያ፣ ሮድሪ፣ ፋቢያን ሩዪዝ፣ ኦልሞ፣ ላሚን ያማል፣ አሌክስ ባይና እና ኦያርዛብልን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አካትታለች፡፡
በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በኩል ኪሊያን ምባፔ፣ ኦሊሴ፣ ዴምቤሌ፣ ባርኮላ፣ ራቢዮት፣ ቹሃሚኒ፣ ዲኜ፣ ኡፓሚካኖ፣ ሳሊባ፣ ኩንዴ እና ማይግናን በቋሚ አሰላለፍ ወደ ሜዳ የሚገቡ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሸናፊ በፍጻሜው ከአርጀንቲና እና እንግሊዝ አሸናፊ ጋር ለዋንጫው ይፋለማል፡፡
14/07/2026
ቤሺክታሽ ሊያንድሮ ትሮሳርድን ከአርሰናል አስፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱርኩ ክለብ ቤሺክታሽ ቤልጂየማዊውን የፊት መስመር ተጫዋች ሊያንድሮ ትሮሳርድ ከአርሰናል አስፈርሟል፡፡
ቤሺክታሽ ለትሮሳርድ ዝውውር 20 ሚሊየን ዩሮ ለሊጉ ሻምፒዮን አርሰናል መክፈሉ ተመላክቷል፡፡
የ31 ዓመቱ ተጫዋች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከአርሰናል ጋር የሊጉን ዋንጫ ማሳካቱ ይታወሳል፡፡
ተጫዋቹ ለአርሰናል በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 174 ጨዋታዎች 70 የግብ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ሊያንድሮ ትሮሳርድ በ2023 ከብራይተን አርሰናልን በ27 ሚሊየን ፓውንድ መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡
14/07/2026
ማንቼስተር ዩናይትድ ዌልሳዊውን ግብ ጠባቂ ካርል ዳርሎውን አስፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ ዌልሳዊውን ግብ ጠባቂ ካርል ዳርሎውን ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል።
የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በሊድስ ዩናይትድ ቤት ያሳለፈውን ግብ ጠባቂ ማንቼስተር ዩናይትድ በነጻ ዝውውር የግሉ አድርጎታል።
የ35 ዓመቱ ግብ ጠባቂ በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት እስከ ፈረንጆቹ 2028 ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
ከአልታይ ባይንደር ጋር እንደሚለያይ የሚጠበቀው ማንቼስተር ዩናይትድ ካርል ዳርሎውን ለሰን ላሜንስ ተጠባባቂ ለማድረግ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።
ካርል ዳርሎውን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ለሊድስ ዩናይትድ በሊጉ 22 ጨዋታዎችን አድርጓል።
14/07/2026
ፈረንሳይ ከስፔን - የፍጻሜ ተፋላሚ ለመሆን…
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የ2026 የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት መደረግ ይጀምራሉ፡፡
በዚህም መሰረት ምሽት 4 ሰዓት ላይ ፈረንሳይ ከስፔን የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ለዋንጫው ቅድመ ግምት ካገኙት ከሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የአንዳቸው ጉዞ ዛሬ ምሽት የሚያበቃ ይሆናል፡፡
ፈረንሳይ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እስካሁን ድረስ ከሴኔጋል፣ ኢራቅ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፓራጓይ እና ሞሮኮ ጋር ተገናኝታ ሁሉንም ጨዋታዎች አሸንፋለች፡፡
በአሰልጣኝ ዲዴ ዴሻምፕ የምትመራው ፈረንሳይ እስከ ሩብ ፍጻሜ ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች 16 ግቦችን ተጋጣሚዎቿ ላይ አስቆጥራ የተቆጠረባት ሁለት ግብ ብቻ ነው፡፡
በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በኩል ኪሊያን ምባፔ፣ የባሎንዶር አሸናፊው ኦስማን ዴምቤሌ እና ኦሊሴ አስደናቂ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
ኪሊያን ምባፔ 8 ግቦችን በማስቆጠር የ2026ቱን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃን ከሊዮኔል ሜሲ ጋር በጋራ እየመራ ሲሆን÷ በተጨማሪም ሦስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
ኦስማን ዴምቤሌ ደግሞ አምስት ግቦችን አስቆጥሮ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡
ሌላኛው የብሔራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ኦሊሴ አምስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን÷ በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ በርካታ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻቶ በማቀበል ቀዳሚው ተጫዋች ነው፡፡
በ2018 እና 2022 የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረችው ፈረንሳይ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ውድድር የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ለመገኘት የምታደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው
ፈረንሳይ በፈረንጆቹ 1998 እና 2018 የዓለም ዋንጫን ያሳካች ሲሆን ÷ ለሦስተኛ ጊዜ በመድረኩ ሻምፒዮን ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ትፋለማለች፡፡
ሌላኛዋ ለዋንጫ የተገመተችው ተጋጣሚዋ ስፔን በፈረንጆቹ 2010 በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ማሳካቷ ይታወሳል፡፡
ስፔን በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እስካሁን ድረስ ከኬፕ ቨርዴ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኡራጓይ፣ ኦስትሪያ፣ ፖርቹጋል እና ቤልጂዬም ጋር የተገናኘች ሲሆን÷ አምስቱን አሸንፋ ከኬፕ ቨርዴ ጋር ብቻ አቻ ተለያይታለች፡፡
ስፔን እስካሁን ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቿ ላይ 11 ግቦችን አስቆጥራለች፤ የተቆጠረባት ደግሞ አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡
ለስፔን ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አራት ግቦችን ያስቆጠረው እና አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ኦያርዛባል በጨዋታው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡
ተቀይሮ ወደ ሜዳ በመግባት ልዩነት እየፈጠረ የሚገኘው ስፔናዊው ተጫዋች ሜሪኖ በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ስፔን ከ2010 በኋላ በድጋሚ በመድረኩ ለመንገስ የምታደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች አሸናፊ ከእንግሊዝ እና አርጀንቲና አሸናፊ ጋር ለዋንጫው ይፋለማል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ