08/01/2026
.."እንጋባ" ሲል ጠየቃት አሳምነው። አልተቀበለችውም አስማሩ። "ወንድምና እህትነቱ ይበልጣል" አለችው። ተስማሙ።
ቤቷ እየመጣ ይጠይቃታል። ቡና ታፈላለች ይጠጣሉ፣ ካላት ታቀርባለች ይበላሉ። አወግተው ይለያያሉ። የትዳር ነገር ዳግም አልተነሳም።
አሳምነው አንድ ቀን በጠራራ ፀሀይ መጣ። እንደመጣ የደረበውን ሹራብ አውልቆ አስቀመጠ። ስለ ሙቀቱ ብዙ አውርተው ተለያዩ።
አስማሩ አሳምነው ረስቶት የሄደውን ሹራብ ልብሷን ስታጥብ አጠበችለት። ዳግም ሲመጣ ደርቦ ደራርቦ ነበርና የሚያወልቀው እንጂ የሚደርበው ልብስ አላስፈለገውም። ጃኬቱን አውልቆ ሄደ። አስማሩ እሱንም አጥባ አኖረችው። ሱሪውን ደርቦ መጣ "ወበቀኝ!" አወለቀው።
አስማሩ አጥባ አኖረችው፣ ካፖርቱን ጥሎ ሄደ፣ አጥባ አኖረችው። አንድ ቀን በጠራራ ፀሀይ ብርድ ልብሱን ለብሶ መጣ፣ አስማሩ "ምነው?'' አለችው። "በጠራራ ፀሀይ ብርድ ሆዴ ገባ'' አላት።
"ምች ይሆናል" አለችው። የምች መድኃኒት ብታሽለት ተሻለው። ሲሻለው ብርድ ልብሱ አላስፈለገውም ጥሎት ሄደ። አስማሩ አጥባ አኖረችው፡፡
ትንሽ ቆይቶ፣ ፍራሹን ተሸክሞ መጣ።
"ምነው?" አለችው።
"ላሳድሰው መሄዴ ነው። አይቼሽ ልለፍ ብዬ ነው'' አላት። አመነችው።
ጨዋታው ደራ፣ ፍራሹን ረስቶት ሄዶ ኖሮ እኩለ ሌሊት ቢመጣ አስማሩ ቦታ ስላጣች ፍራሹን ፍራሿ ላይ ደርባው ደረሰ። ያኔ "ተነሽ" ከማለት "ጠጋ በይ'' ማለት ቀልሎ ተገኘ። ጠጋ አለች ....... ጨዋታው ደራ!
(በአለማየሁ ገላጋይ )
08/01/2026
በመኖር አጸድ ውስጥ
(በእውቀቱ ስዩም)
ጊዜ ከሰው መሀል- መርጦ ሲያቀማጥል
ማጣት አለ ደሞ፥
የወለዱትን ልጅ፥ ጉድፍ ላይ የሚያስጥል
በተፈሰከ ቀን፥ ጾምን የሚያስቀጥል።
እድልና ትግል በሚጫወቱበት
በደልዳላው ስፍራ
አለቃና ጭፍራ-
-ቃል ሲለዋወጡ፥ ውልና መሀላ
“አብረን እናድጋለን” ቢባል ለይስሙላ
ወንዙን ሳያጎድል ፥ሐይቁ መች ሊሞላ፤
ጸሐይ ብትወጣ
ፍጥረት በጠቅላላው ጸጋዋን ቢቀበል
የደመናም ጠበል፥
ለሁሉ ቢደርስም
አንደኛው አያድግም፥ አንዱን ሳያከስም።
የንባብ አለም 📚📚
05/01/2026
☯የማንነት እውነት
✍ደምስ ሰይፉ
“You’ll never know who you are unless you shed who you pretend to be. ” ― Vironika Tugaleva
⚡️በዙሪያችን ያለው ደመና በውስጣችን ያለውን ጸሐይ ከልሎታል… የየዕለታችን አመድ የመነሻችንን ፍም አዳፍኖታል… የአስተዳደጋችን ቅኝት የዕይታ አድማሳችንን ኮድኩዶታል፣ የአስተምሯችን ስሪት፣ የየቤተእምነታችን መሰረት፣ የአካባቢ፣ የሃገር፣ የሚዲያና የአብሮ ውሎ ሸንጓችን ጨለማ የማንነታችንን ግዝፈት ውጦታል… ትልቁን ምስል ለማየት ስለተሳነን ባየነው ልክ ራሳችንን ሰርተናል… በምልዓት ማየት ስላልጀመርን ለሽንቁር ማንነት ራሳችንን አሳልፈን ሰጥተናል… ነባሩን ዘዬ ስላልፈተሽን አዲስ መንገድ ማየት አቅቶናል… የነገሩንን ስላመንን የሆነውን መጠየቅ ትተናል… አይቻልም ስላሉን አለመደፈሩን ተቀብለናል… እናም ዛሬ ራስዳሽኑ ማንነት በኮረት ጥላ ውስጥ ተጨልሟል…
⚜የማንነትን ጉዳይ… እንደየ ጥናት መስኩ ሃቲት፣ እንደየ መንግስታቱ ውልደት፣ እንደየ ማሕበረሰቡ ነባር ትውፊት፣ እንደየ ሐይማኖታቱ መፃሕፍት እንጂ እንደ ጥልቁ ማንነታችን ምንነት ለመተንተን ሞክረን አናውቅም… ለኛ ማንነት ማለት ብዙዎች የሚያቀነቅኑት ምንነት ነው – ከየልባችን የምንመክረው ዘላለማዊ ወግ አይደለም… ማንነት ለኛ ከመሰሎቻችን የተዋስነው የአደራ ዕቃ ነው – በነፍሳችን ሹክሹክታ ስምረት የሚሰራ ሁሉአዊ መልክ አይደለም… ማንነት ለኛ ከመሆን በኋላ በሆነ ሁነት ውስጥ የሚቀነበብ ወቅታዊ ነው – ከመሆን በፊት በነበረ፣ ባለና በሚኖር ምንጭ ላይ የቆመ ዘላለማዊ አይደለም…
🔆የልኬታችንን ምልዓተ ዓለምነት እንዳናይ አዚም ያደረገብን ማነው?… የምንጫችንን አልፋ እንዳናውቅ ነገር የሰራብን ማነው?… ከጥልቅነታችን የመሰረት ወለል የነቀለን ማነው?… በአንድነት አውድማችን ላይ እልፍነትን ያበራየው ማነው?… በስክነት ጉባኤያችን ውስጥ ጩኸት የዶለው ማነው?… እውነትን ከምናይበት ማማ ላይ ጽልመት የጋረደብን ማነው?…
⚜‘አንተ ማነህ?’ ላለን ሁሉ ማንነት ያልሆነ ማንነት ስንነግር ቆይተናል… ስማችን ያልሆነ ስም፣ ሃገር ያልሆነ ሃገር፣ ቀለም ያልሆነ ቀለም፣ ልክን የማይገልጽ ልኬት፣ ተናጥሎን የሚሰብክ ማንነት፣ ብስለትን የማይገልጽ ዕድሜ፣ ምንምነትን የሚያረቅ ታሪክ፣ … ወዘተ… በቀቀናዊ ኑረት…
⚡️ከመሆን በፊት የሆንከው መሆን ዘላለማዊ፣ ከመሆን በኋላ የሆንከው ሁነት ጊዜያዊ ነው… ዜግነትህ፣ ብሔርህ፣ የትምህርት ደረጃህ፣ ስራህ፣ መደብህ፣ የትውልድ ቦታህ፣ ቤተሰብህ፣ ሐይማኖትህ… ማናቸውም በ ‘እኔ’ ና ‘የኔ’ ቁናነት የሚሰፈሩ ነገሮችህ ማንነትህ አይደሉም… የትኛውም፣ ከእስከ አልባው ሕዋ በተናጥሎ የሚያስቀምጥህ ሃሳባዊውም ሆነ ቁሳዊ ምንትስ ማንነትህ አይደለም… ያንተ ማንነት የሌላውም ማንነት ነው… የእኔ፣ የእርሱ፣ የእነርሱ የሚባል ማንነት የለም… ማንነት አንድና ዘላለማዊ ነው… ዘላለማዊ ማንነት ስላለህ ዘላለምህ ውስጥ ሞት እንኳ የለም…
🔑 በ’እኔታ’ እና ‘አንተታ’ መገለጥ /Subjective manifestation/ ውስጥ እንመላለስ እንጂ የምንጫችን አንድነት /Oneness/ የሁለንተናችን አንድነት ነው… ይህም በሰው፣ በእንስሳ፣ በተክል፣ በፕላኔት፣ በጠፈር፣ በሕዋ… በሚታየውና በማይታየው ዓለም ውስጥ ባሉ መገለጦች ውስጥ ሁሉ ያለ አንድነት ነው… ሕብረት፣ ጋርዮሽ፣ ጥምረት፣ ሕብራዊነት፣ ትብብር አይደለም አነድ-ነት ነው… አንድ ላይ መሆን አይደለም አንድ ብቻ መሆን ነው… Self ውስጥ ቁጥር የለም… በቃ ‘መሆን’ Being ብቻ ነው ያለው…
💫ራማና ማሀርሺ እንደነገረን “The Self is beyond duality. If there is one there will also be two. Without one there are no other numbers. The truth is neither one nor two. It is as it is.”
🔆ማንነት አለኝ የምትለው አይደለም – የሆንከው እራሱ ነው… Possession በማንነት ውስጥ ቦታ የለውም… አንተነትህ ከማንነትህ የተነጠለ አይደለም – ማንነትህ ነው አነተነትህ… ማንነትህ ቅርጽ፣ ቀለም፣ መስፈሪያ፣ ድንበር አልያም ጠገግ የለውም – በሁሉ ያለ፣ በሁሉም የሚኖር ነው…
💫“All that we have to do is to give up identifying the Self with the body, with forms and limits, and then we shall know ourselves as the Self that we always are.” Ramana Maharshi
⚜አንተ ውስጥ ‘ሌላው’ አለ – ‘ሌላው’ ውስጥም አንተ አለህ… “Quantum Physics reveals thus reveals a basic oneness of the universe” – Erwin Schrödinger
💫 አንስታይን በበኩሉ ይህን ይላል … “A human being is part of the whole, called by us ‘Universe’; a part limited in time and space. He experiences himself, his thoughts and feelings as something separated from the rest—a kind of optical delusion of his consciousness. This delusion is a kind of prison for us, restricting us to our personal desires and to affection for a few persons nearest us. Our task must be to free ourselves from this prison.”- Albert Einstein
🔆ስለማንነትህ እንዲገባህ ማንንም አትጠይቅ… የማንነትህን ልኬት በሌሎች ግንዛቤ ውስጥም አትሻ… ከራስህ ጋር አውጋ! ወደውስጥህ ተመልከት…
⚡️ከውጭ የምታየው ሁሉ የውስጥያህ ነጸብራቅ ነው… አንተ ሕዋ ውስጥ ሳይሆን ሕዋው ነው አንተ ውስጥ ያለው እንደማለት…
💫“You are not IN the universe; you ARE the universe, an intrinsic part of it. Ultimately you are not a person, but a focal point where the universe is becoming conscious of itself. What an amazing miracle.” ― Eckhart Tolle, ‘A New Earth’
🔆ነፍስህ እስካላዜመችው ማንነት አይገባም… ከአዕምሮ ባርነት እስካልተላቀቅህ መሆን አይገለጽም… ወደ ውስጥ እስካልዘለቅህ ከራስህ ጋር አትገናኝም
🔑ልብህን ጠይቅ ይመለስልሃል!! የማንኛውም ጥያቄህ መልስ ማንነትህ ውስጥ አለ… ማንነትህን የማወቅህ ቅጽበት ውስጥ ደግሞ ደስታ – ዘላለማዊ ደስታ… እ-ፎ-ይ-ታ!!!
መልካም አሁን
⚜🔑⚜🔑⚜🔑⚜🔑⚜
ውብ ምሽት❤
29/12/2025
🌀የህይወት ጎበዝ ሁን❤
ከክፍል አንደኛ መውጣትህ፣ ሰቃይ ተማሪ መሆንህ፣ በማዕረግ መጨረስህ- በህይወትህ ስኬታማ እንድትሆን ዋስትና ይሆንሃል ማለት አይደለም። በኢኮኖሚክስ በማዕረግ ልትመረቅ ትችል ይሆናል፣ ይሁንና ከሁሉ የተሻለ ገቢ ታገኛለህ ማለት አይደለም። ጎበዝ የህግ ተማሪ ነበርክ ማለት ጎበዝ ጠበቃ ትሆናለህ ማለትም አይደለም። ይሀውልህ፤ ህይወት- ፅንሰ ሃሳብን (concept) ከመረዳት፣ ነገሮችን ከማስታወስ (Memoriase ize)ና፣ ፈተና ላይ ከመተግበር (reproduce) በላይ አቅም ትፈልጋለች።
• ትምህርት ቤቶች፣ ሰዎችን 'ለማስታወስ ችሎታቸው' ዕውቅና ሲሰጡ፤ ህይወት ግን፣ ሰዎችን 'ለተግባራቸው' ዕውቅና ትሰጣለች።
• ትምህርት ቤቶች ማስጠንቀቂያ (caution) ሲሰጡ፤ ህይወት ግን ድፍረትን ትሰጣለች።
• ትምህርት ቤቶች በ"ደንብ" የሚኖሩትን ሲያመሰግኑ፤ ህይወት ግን ደንብን ጥሰው፣ አዲስ ህግን ያስቀመጡትን ታወድሳለች።
ታዲያ ሰዎች በትምህርት ቤት ጠንክረው መማር የለባቸውም እያልኩ ነው?- በፍፁም። መማርህ የግድ ነው። ይሁንና "አንደኛ" ለመውጣት ብለህ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ መስዋእት አታድርግ እያልኩህ ነው።
ያንተ ጉብዝና በ10ኛ ክፍል ውጤት አዘለለህ፣ በ12ኛ ክፍል ውጤት አስፈነደቀህ፣ በከፍተኛ ትምህርት ውጤትህ አስወደሰህ...ከዛስ? - ከዛማ ቅጥረኛ ሆነሃል። የወር ደሞዝ ትጠብቃለህ፣ ፍቃድህ በአለቃህ (ሰቃይ ተማሪ ባልነበረው) ላይ ወድቋል።
ትላንት ግብረገብ ላይ ጥሩ ሆኖ በሌላ ዘርፍ ግን ደክሞ የናቅከው ተማሪ፣ ዛሬ የሞራል አለቃህ (የሃይማኖት ሰው) ሆኖ ይመራሃል፤
ትላንት ስነ-ዜጋ ላይ በርትቶ በሌላው ግን ደክሞ የተቸኸው ተማሪ፣ ዛሬ ባለስልጣን ሆኖ አጠገቡ ለመድረስ የምትናፍቀው ሰው ሆኗል፤
ትላንት ስእልና ሙዚቃ ላይ ጊዜውን እያጠፋ በሌላው ግን ስለደከመ የናቅከው ተማሪ፣ ዛሬ የምታደንቀው አርቲስት ነው፤
ትላንት ሽቦ ሲወጥር፣ እንጨት ሲቆርጥ- ከነጓደኞችህ ያሾፍክበት ተማሪ፣ ዛሬ እርሱ ጋር ለመቀጠር በብርቱ የምትፈልገው የትልቅ ኢንዱስትሪ ባለቤት ሆኗል።
የትምህርቱ ጎበዝ በህይወት ጎበዞች ተበልጠሃል። ዛሬ ላይ ቆመህ የነርሱን ህይወት ትናፍቃለህ። ደስታህ በደስታቸው፣ ሀዘንህ በሀዘናቸው ላይ ተመሥርቷል። አሁንም ግን ጊዜው አልረፈደም። እስትንፋስህ እስካለች ህይወት ትቀጥላለች። ራስህን በክፍል አትገድበው፤ በምግባርህ ጎልተህ ውጣ፤ የመሪነቱንም ድርሻ ውሰድ።
እስቲ የንግድ ሥራ ጀምርና አይሳካልህ፣ ብዙ አማራጮችን ትቀስምበታለህ። ለምርጫ ተወዳደርና ተሸነፍ፣ የፓለቲካ ሳይንቲስት የማያስተምርህን ነገር ያስተምርሃል። ውስጥህ ያለውን ተሰጥኦ አውጣውና ይታይ፣ አጎልብተውም፤ በሙያህ ዘርፍ ብቻ ሳትገደብ መፅሐፍትን አንብብ፣ ያመንክበትን ነገርም አድርግ። በቃ! ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ከማሰብ ይልቅ፣ ጎበዝ ሰው ለመሆን አስብ። ትምህርት ቤትህን አለምህ አታድርገው፣ አለምህን ትምህርት ቤትህ እንጂ!።
ወደፊት ተራመድ፤
ፓለቲካውን ሞክር፤
ኪነጥበቡን ሞክር፤
ግብርናውን ሞክር፤
ንግዱን ሞክር፤
በቃ ተጨማሪና አዲስ ነገር ሞክር!!
ልብ በል፤ ፈጣሪም የሚረዳው የሚሞክሩትን ነው። ከሰማይ ይልቅ በምድር ያስቀመጠህም በአላማ ነው። የምትበርበት ክንፍ ያልሰጠህ አውሮፕላን ሰርተህ እንድትበር፣ ተሽከርካሪ እግር ያላደለህ መኪና ሰርተህ እንድትሽከረከር ነው።
ከርሱ ዘንድ፣ በየቀኑ የሚሰጥህን ዕድል ያለመሰሰት ተጠቀምበትና የህይወት ጎበዝ ሁን!
ውብ አሁን❤
28/12/2025
🔵ሕይወት አዙሪት ናት
ሕይወት አዙሪት ናት፡፡ ረጅም ርቀት የተጓዝክ ቢመስልህም የምትጨርሠው ከጀመርክበት ነው፡፡
፨ ራቁትክን ትወለዳለህ፤ እርቃንህን ወደመቃብር ትወርዳለህ ፡፡
፨ በጥርስ አልባው ድድህ እየጋጥክ ትጀምራለህ፤ ጥርሱን ባረገፈው ድድህ እያልጎጠጎጥክ ትጨርሳለህ ።
፨ የሕይወትን ትግል እየዳህ ትጀምራለህ፤ አጎንብሠህ ትጨርሳለህ፡፡
ዘመንም ተምኔታዊ ነው፡፡
መስከረም ጥቅምት ብሎ ያስጀምርህና መስከረም ብሎ ይመጣብሃል፡፡ ሠኞ ማክሠኞ ብለህ ተጉዘህ፤ እንደገና ሠኞ ትላለህ ፡፡ ሕይወት አዙሪት ናት! መጀመሪያህ መጨረሻህ ነው፡፡ የጀመርክበትን አትርሳ፤ መጨረሻህ ነውና፡፡ የጀመርክበትን አትናቀው፤ ትጨርስበታለህና፡፡ ተራ ሠው ሆነህ ትጀምራለህ፤ ተምረህ ዕውቀት ብትጨምርም፤ ነግደህ ሃብት ብታገኝ፤ ተሹመህ በሕዝብ ላይ ብትሠለጥን፤ ክቡረ ክቡራን ሆነህ የወርቅ ካባ ብትለብስ፤ የምትጨርሠው እንደተራ ሠው አፈር ለብሠህ ነው፡፡
ልብ በል! ባለማወቅ ትጀምራለህ፤ በመዘንጋት ትጨርሳህ፡፡ ዕውቀት አላመጣህምና ዕውቀትም ይዘህ አትሄድም፡፡ በለቅሶ ትጀምራለህ፤ በጭንቅ ትጨርሳለህ፡፡ በሠው እቅፍ ትጀምራለህ፤ በሠው ሸክም ትጨርሳለህ፡፡
ልደትህ ከሞትህ በምን ይለያል? ሞትህስ ከልደትህ በምን ይከፋል? ሕይወት መጀመሪያዋና መጨረሻዋ አንድ ነው፡፡ በዚህ የተነሣ ጠቢቡ እንዳለው ሁሉም የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ ልብ በል! የዓለም ከንቱነት ግን ውበትዋ ነው፡፡ ዓለም አዲስ ነገር ቢኖራት እኛን እንዴት በፀፀተን፤ ሞት የእውነት መጨረሻ ቢሆን እንዴት በቆጨን!!
‹‹ርቀህ የሄድክ ቢመስልህም፤ ትልቅ ክብ ሠርተህ ተመልሠህ እዚህ ትመጣለህ፡፡ ዋናውን ተግባርክን ግን እስካሁን አልጀመርከውም፡፡››
፧
ምንጭ ፦ ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ
(መርበብት - ከገጽ 314 - 315)
ያንብቡት ይወዱታል
🔹🔹🔹🔹🔹🔹🔹🔹🔹🔹🔹🔹