20/05/2026
አስቶንቪላ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ
አስቶንቪላ ፍሬይቡርግን 3ለ0 በማሸነፍ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን አረጋገጠ።
በቤሺክታሽ ፓርክ በተደረገው ጨዋታ የእንግሊዙን ክለብ ድል ያበሰሩ ግቦች ዩሪ ቲሊማንስ ፣ ኤሚ ቡንዲያ እና ሞርጋን ሮጀርስ አስገኝተዋል።
የአስቶንቪላን የበላይነት መግታት ያልቻለው የጀርመኑ ክለብ ፍሬይቡርግ የመጀመሪያ የአውሮፓ ውድድር የፍፃሜ ጨዋታው በሽንፈት ተደምድሟል።
አስቶንቪላ በአውሮፓ መድረክ ሲነግስ ከ44 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ቪሊ እኤአ ከ1982 ባየርን ሙኒክን አሸንፎ የዩሮፒያን ካፕ (አሁን ቻምፒየንስ ሊግ) ካሸነፈ በኋላ ዋንጫ የማንሳት እድል አልነበረውም።
"የዩሮፓ ሊግ ንጉስ" የሚል ቅፅል ስም ያገኙት የአስቶኝቪላው አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬይ አምስተኛ ዋንጫቸውን አንስተዋል። ስፔናዊው አሰልጣኝ ከዚህ ቀደሞ ከሲቪያ ጋር ሦስት ፣ ከቪያሪያል ጋር ደግሞ አንድ ጊዜ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ማሸነፋቸው ይታወቃል።
20/05/2026
ኢትዮጵያ ቡና ወደ ድል ተመለሰ
ኢትዮጵያ ቡና በ33ኛ ሳምንት የሊግ መርሐግብሩ ፋሲል ከነማን ገጥሞ 2ለ1 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አቡበከር አዳሙ በፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ አሸናፊ በጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናን የማሸነፊያ ግቦች አስቆጥረዋል። ኪሩቤል ዳኜ የፋሲል ከነማን ብቸኛ ግብ አስመዝግቧል።
ከአራት ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ድል ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 46 አድርሷል። በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ጨዋታውን የተሸነፈው ፋሲል ከነማም በተመሳሳይ 46 ነጥብ ይዟል።
20/05/2026
መቐለ 70 እንደርታ ወሳኝ ድል አሳካ
በ33ኛ ሳምንት የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐግብር ሸገር ከተማን የገጠመው መቐለ 70 እንደርታ 1ለ0 አሸንፏል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ቦና አሊ የመቐለን ግብ 90+1 ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።
ወራጅ ቀጠና የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 34 አሳድጓል። ሁለት ተከታታይ ጨዋታ የተሸነፈው ሸገር ከተማ 40 ነጥብ አለው።
19/05/2026
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ተጋጣሚዎቹን ለይቷል
የ2027 አፍሪካ ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ድልድል በግብፅ ካይሮ ይፋ ሆኗል።
በቅድመ ማጣሪያው ሳኦቶሜን ያሸነፉት ዋልያዎቹ ከሴኔጋል ፣ ሞዛምቢክ እና ሱዳን ጋር በምድብ 10 ተደልድለዋል።
በሦስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኬንያ ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛኒያ የሚዘጋጀው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ መስከረም ወር ላይ ይጀምራሉ።
19/05/2026
ፔፕ ጋርዲዮላን በኢንዞ ማሬስካ?
ትናንት ምሽት የተሰማው ዜና ከማንችስተር ሲቲ አልፎ በመላው ዓለም ያሉ የእግርኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ የሳበ ነበር። በተአማኒነታቸው የተወደሱ በርካታ የእንግሊዝ ብዙሃን መገናኛ ፔፕ ጋርዲዮላ የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅ የማንችስተር ሲቲ እህል ውሃው ያበቃል አሉ።
መቼ የሚለው ካለሆነ በስተቀር ፔፕ 10 ዓመታት የነገሰበትን ዙፋን ለሌላ ማስረከቡ የማይቀር ነው። የበርካቶችን ቀልብ የሳበው ፔፕ ምንም ፍንጭ አለመስጠቱ ይመስላል። የ55 ዓመቱ ስፔናዊው አሰልጣኝ ከጋዜጠኞች የሚቀርብለትን “ይህ የመጨረሻ የውድድር ዓመትህ ሊሆን ይችላል?’’ ጥያቄን የሚያልፈው ቀሪ የአንድ ዓመት ውል አለኝ በሚል ነበር።
ማንችስተር ሲቲ ይህ እንዲሆን ትልቁ ምኞቱ ነበር። ፔፕ እንዳለው ውሉን ቢጨርስ ይመርጣሉ ፤ ነገር ግን እርሱን መተካት የሚያስችል ስራ ቀድመው አከናውነዋል።
ታላቁ አሰልጣኛቸው እንዲቆይ ቢመኙም መጨረሻው መቃረቡን ቀድመው ተገንዝበዋል። ለዛም ነው የቀድሞ የሲቲ ወጣት ቡድን እንዲሁም የጋርዲዮላ ረዳት አሰልጣኝ የነበረው ኢንዞ ማሬስካን ለመሾም የተቃረቡት።
ፔፕ ጋርዲዮላ ከማንችስተር ሲቲ አልፎ በእንግሊዝ እግር ኳስ ውስጥ እንደ አብዮተኛ ይቆጠራል። በሁለት አስርተ ዓመታት የውሃ ሰማያዊዎቹ ቤት ቆይታው 20 ዋንጫዎቹን አሸንፏል። ከዋንጫዎቹ ብዛት በዘለለ ድሎቹ የመጡበት መንገድ በርካቶች የእርሱ ተከታይ እንዲሆኑ አድርጓል።
በእንግሊዝ ታችኛው ዲቪዚዮን የሚጫወቱ ክለቦች ሳይቀር አጨዋወቱን ኮርጀዋል። አንዳንዶች በእንግሊዝ በፈጠረው ተጽዕኖ ምክንያት ከሰር አሌክስ ፈርጉሰንም በላይ የምንጊዜውም ምርጥ አሰልጣኝ መባል አለበት የሚሉ በርካታ ናቸው።
100 ነጥብ አምጥቶ ዋንጫ ያነሳ ፤ በእንግሊዝ ሆኖ የማያውቅ አራት ተከታታይ የሊግ ዋንጫ ያሸነፈ ሌሎች በርካታ ተዓምሮችን ያሳየ አሰልጣኝ የምንጊዜም ምርጥ መባል እንዳለበት ይከራከራሉ።
ይህን ምጡቅ አሰላጣኝ መተካት ለማንችስተር ሲቲ ፈታኝ ቢሆንም ለጊዜው በእርሱ ስር የተማረውን ኢንዞ ማሬስካን መርጠዋል። ጣልያናዊው አሰልጣኝ የሲቲን ቤት በደንብ ጠንቅቆ ቢያውቅም ፔፕን መተካት ፈታኝ ይሆንበታል። ሌስተር ሲቲን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደግ እና በቼልሲ ያገኛቸው የኮንፍረንስ እና የዓለም ክለቦች ዋንጫ በቂ ላይሆን ይችላል። ይህ ሁሉ ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው።
ለጊዜው የፔፕ ጋርዲዮላም ሆነ የማንችስተር ሲቲ ሙሉ ትኩረት ቀሪ ሁለት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ይሆናል።
በሸዋንግዛው ግርማ
19/05/2026
ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ አቻ ተለያዩ
በ33ኛው ሳምንት ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም ቀን 7 ሰዓት ላይ በተደረገው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ ነው ጨዋታቸውን ያጠናቀቁት፡፡
19/05/2026
ሰበር ዜና | ኢንዞ ማሬስካ የማንስተር ሲቲ አሰልጣኝ ለመሆን ተስማሙ!
ጣልያናዊው አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ ፔፕ ጋርዲዮላን በመተካት አዲሱ የማንቸስተር ሲቲ ዋና አሰልጣኝ ለመሆን ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተረጋግጧል።
ማሬስካ በኢቲሃድ ስታዲየም የ3 ዓመታት ኮንትራት እንደሚፈራረሙ ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ዘግቧል።
ማሬስካ ቀደም ሲል በማንቸስተር ሲቲ በፔፕ ጋርዲዮላ ስር በረዳት አሰልጣኝነት በስኬት መስራታቸው ይታወሳል። የቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኝ አሁን ወደ ቀድሞ ቤታቸው በዋና አሰልጣኝነት ለመመለስ ተቃርበዋል።
19/05/2026
ቦርንማውዝ ከማንቼስተር ሲቲ
በ37ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ማንቼስተር ሲቲ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ምሽት 3 ሰዓት ከ30 ላይ ቦርንማውዝን ይገጥማል፡፡
በአሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
ማንቼስተር ሲቲ በምሽቱ ጨዋታ ነጥብ የሚጥል ከሆነ አርሰናል የ38ኛ ሳምንት ጨዋታውን ሳያደርግ የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ቦርንማውዝ በበኩሉ የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ቦታን ለማግኘት የሚያደርገው ፉክክር በጨዋታው ይጠበቃል፡፡
16/05/2026
ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን አሸነፈ።
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ፋሲል ከነማን ከአዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን 3ለ1 ነው ያሸነፈው።
የፋሲል ከነማን የማሸነፊያ ግቦች በ35ኛው እና በ67ኛው ደቂቃ ታምራት ኢያሱ እና 90+9 ቃልኪዳን ዘላለም አስቆጥረዋል።
አዳማ ከተማን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ ደግሞ በ12ኛው ደቂቃ የፋሲል ከነማው አብዱልአዚዝ አማን በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል።
16/05/2026
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አሸነፈ::
በ32ኛ ሳምንት የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ1 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኮንኮኒ ሀፊዝ እና እንዳልካቸው ጥበቡ የወልዋሎን ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል። አቤል ሀብታሙ የኤሌክትሪክን ብቸኛ ግብ ያስገኘ ተጫዋች ነው።
ወልዋሎ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 39 አድርሷል። በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ሽንፈት የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ 45 ነጥብ ይዟል።
16/05/2026
ማንችስተር ሲቲ የኤፍ ኤ ካፕ አሸናፊ ሆነ
ማንችስተር ሲቲ ቼልሲን በማሸነፍ ለስምንተኛ ጊዜ የኤፍ ኤ ካፕ አሸናፊ ሆኗል።
በዌምብሌይ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አንቷን ሴሜንዮ ያስቆጠረው ግብ ማንችስተር ሲቲን ባለድል አድርጓል። ሲቲም በአጠቃላይ ያሸነፋቸውን የኤፍ ኤ ዋንጫዎች ስምንት አድርሷል።
የፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን በውድድር ዓመቱ ያሸነፈው ሁለተኛ ዋንጫውም ሆኗል። ሲቲ በካራባኦ ካፕ አርሰናልን አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።
ፔፕ ጋርዲዮላ በማንችስተር ሲቲ የ10 ዓመታት ቆይታው 20 ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።
አሁንም በፕሪምየር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ሲቲ የፊታችን ረቡዕ ከቦርንማውዝ ጋር ይጫወታል።
በጊዜያዊ አሰልጣኝ ካሉም ማክፋርሌን የተመራው ቼልሲ በርካቶች ከጠበቁትም በላይ ቢፎካከርም ማሸነፍ አልቻለም። የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በመጨረሻ ካደረጋቸው አራት የኤፍ ኤ ካፕ ፍፃሜ ጨዋታዎች አንዱንም አላሸነፈም።