13/07/2026
በአዳማ ከሰሞኑ አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መካሄዱ ታወቀ
በፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አዳም ፋራህ የተመራውና ከየክልሉ የተወጣጡ ከ300 በላይ አባላት የተሳተፉበት በዚህ ስብሰባ ላይ፤ ፓርቲው ለሀገራዊ ምክክሩ እንደ አቋም የያዛቸውና ሊተገበሩ ይገባል ያላቸው አጀንዳዎች ቀርበው ሰፊ ክርክር ተካሂዶባቸዋል። በተለይም ለሀገራዊ ምክክሩ የተዘጋጁና አከራካሪ የሆኑ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ሃሳቦች በሁለት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል "የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል" ከሚለው ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ውስጥ "...እስከ መገንጠል" የሚለው ሐረግ እንዲሰረዝ የሚለው ይገኝበታል። በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው "ልዩ ጥቅም" የሚለው ድንጋጌ ቀርቶ ወደ "የጋራ ጥቅም" እንዲቀየር የሚል ሃሳብ ቀርቧል።
አሁን ያለው የክልሎች አወቃቀር ለሀገር አንድነት ስጋት ነው ተብሎ ስለሚታመን፣ ክልሎች በቋንቋና በማንነት ሳይሆን በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና በኢኮኖሚ ትስስር ላይ ተመስርተው እንዲዋቀሩ የሚል አጀንዳ በዋነኝነት ቀርቧል። ከዚህ ጋር ተያይዞም አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች እንዲሆኑና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ውክልና እንዲኖራቸው የሚሉ ነጥቦች ተነስተዋል። በመሬት ባለቤትነት ረገድም መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ መሆኑ ቀርቶ የግል ባለቤትነትን እንዲያካትት፣ ይህም መሬትን እንደ አስፈላጊነቱ ለመሸጥና ለመለወጥ እንዲሁም ለኢንቨስተሮች ዋስትና ለመስጠት እንዲያስችል ማሻሻያ እንዲደረግ ተጠይቋል።
ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል በተለይ "ክልሎች በማንነት ሳይሆን በጂኦግራፊና በኢኮኖሚ ይዋቀሩ" የሚለውን ሃሳብና የኦሮሚያ "ልዩ ጥቅም" ቀርቶ "የጋራ ጥቅም" ይሁን የሚሉትን ነጥቦች የኦሮሚያ ክልል አመራሮች በጽኑ ተቃውመውታል። በሌላ በኩል በሕገ-መንግሥቱ መግቢያ ላይ የሚገኘው "እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች" የሚለው ሐረግ በ"እኛ ሕብረብሔራዊ የኢትዮጵያ ሕዝቦች" በሚል እንዲተካ ፓርቲው አቋም መያዙ ተገልጿል። ይህ ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደው ስብሰባ መረጃዎች ባለፈው ሳምንት በስፋት ሲሰራጩ መቆየታቸው ይታወሳል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
07/07/2026
የኤርትራ መንግስት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ዛሬ በፓርላማ ቀርበው ለሰጡት ማብራሪያ እና በተለይ ከኤርትራ (ሻዕቢያ)፣ ከሕወሓት እና ከሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ላነሷቸው ነጥቦች በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ፈጣንና ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥቷል። ሁለቱ ወገኖች በቀጠናው ሰላምና በጎረቤት ሀገራት ጣልቃ ገብነት ዙሪያ እርስ በርሳቸው ተቃራኒ የሆኑ ክሶችን ሰንዝረዋል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ንግግራቸው በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ወጣቶችን በጉልበት እያፈሱ ለሱዳን ጦርነት "እየሸጡ" መሆኑን ገልጸዋል። "የትግራይ ወጣቶች በማያውቁት ጉዳይ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ህይወታቸውን እያጡ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ድርጊት የህዝቡን መከራ የሚያባብስ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
በተቃራኒው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ለሱዳን ግጭት መባባስ ተጠያቂው የኢትዮጵያ መንግስት ራሱ ነው ሲል ገልጿል። ኢትዮጵያ ለሱዳኑ ፈጣን ደጋፊ ኃይሎች (RSF) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሚስጥራዊ የጦር ሰፈርና ማሰልጠኛ በመስጠት በቀጥታ በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑንና ለዚህም "ግልጽ ማስረጃዎች አሉ" ሲል አጸፋዊ ክስ ሰንዝሯል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በንግግራቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም አይነት "ትንኮሳ" ለመመከት መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። የኤርትራ መንግስት በበኩሉ፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህግጋትንና የቀጠናውን ሀገራት ሉዓላዊነት እየጣሰች ያለችው "የባህር በር ባለቤትነት" በሚል በምታሳየው የግዛት ማስፋፋት ፍላጎት ነው ብሏል። የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ በኩል "ጥቃት አድራሽ" በሌላ በኩል ደግሞ "ተጠቂ" ሆኖ የመቅረብ ድራማ እየሰራ ነው ስትልም ወርፋለች።
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ለክልላዊ ውጥረቶች ኤርትራንና ሕወሓትን ተጠያቂ ሲያደርጉ፤ የኤርትራ መንግስት ደግሞ በተቃራኒው የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው "ያልተረጋጋና ቀስቃሽ" ፖሊሲ ለቀጠናው ሰላም መታወክ ዋና መንስኤ ነው የሚል አቋም ይዟል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
03/07/2026
ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ በትግራይ ክልል ሰሞኑን ተባብሶ የቀጠለው አስገዳጅ ወታደራዊ አፈና በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቁ።
ሚኒስትሩ በይፋ ባስተላለፉት መልዕክታቸው በትግራይ ክልል በተለይም በመቀሌና በተለያዩ ከተሞች እናቶች "ልጆቻችንን አትውሰዱብን" በማለት ተቃውሞ እያደረጉና መንገድ እየዘጉ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ይህ የእናቶች እርምጃ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል። ሚኒስትሩ ይህን ወታደራዊ አፈና እየፈጸሙ ያሉ አካላት ድርጊታቸውን እንዲያቆሙና በቅርቡ በዶ/ር ደብረጽዮን አማካኝነት የጸደቁት አፋኝ መመሪያዎች ሊወገዱ እንደሚገባም በመልዕክታቸው አመልክተዋል።
ዶ/ር አብርሃም በክልሉ የሚታየው ተቃውሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለይም የሚዲያ አካላት፣ የዲያስፓራ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተቃውሞአቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በሚስጥራዊ ስፍራዎች እገታዎች እንደሚፈጸሙና "ልጆቻችንን አሳልፈን አንሰጥም" ባሉ ሽማግሌዎችና ወላጆች ላይ እስር እየተፈጸመ መሆኑን በጽሁፋቸው ገልጸዋል። ይህን መሰሉ ህፃናትን አፍኖ ለሌላ ዓላማ አሳልፎ የመስጠት ድርጊት በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
26/06/2026
የአሜሪካው አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ወደ መቀሌ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ ለምን ተሰረዘ?
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በትግራይ ክልል እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ለማርገብና ዳግም ግጭት እንዳይከሰት ለማድረግ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየት በተደጋጋሚ ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም ለዛሬ ዓርብ ተይዞ የነበረውን ጨምሮ ጉዞው ሳይሳካ ቀርቷል። ለጉዞው መሰረዝ እንደ ምክንያት የቀረቡት፤ አንደኛው በህወሓት በኩል የሚፈለገው የውክልና እውቅና ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የፌደራል መንግሥት ያወጣው የውጭ ጉዳይ መመሪያ ነው።
አምባሳደር ኤርቪን ወደ መቀሌ ሲጓዙ ለማግኘት አቅደው የነበረው፣ በፌደራል መንግሥቱ ሥልጣናቸው የተራዘመውን ጀነራል ታደሰ ወረደን እንደ ክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት፣ እንዲሁም ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን እንደ ህወሓት ሊቀመንበርነት ነበር። ይህ የሆነው አምባሳደሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓመታት በፊት ያወጣውን መመሪያ ለመከተል በመፈለጋቸው ነው።
መመሪያው አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ያለ ቅድመ ማሳወቂያ ወደ ክልሎች እንዳይጓዙና ከክልል አመራሮች ጋር እንዳይገናኙ የሚከለክል ነው።
በዚህ መሠረት አምባሳደር ማሲንጋ ዶ/ር ደብረጽዮንን እንደ ህወሓት ሊቀመንበር፣ ጀነራል ታደሰ ወረደን ደግሞ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊ ለማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው ያሳወቁ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉን አስተዳደር ተቆጣጥረናል የሚሉት በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው አካል ግን እንደ ህወሓት ሊቀመንበር ሳይሆን እንደ ክልሉ መንግሥት ለመወያየት በመፈለጉና አምባሳደሩ ከጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር እንዲገናኙ ባለመፍቀዱ ጉዞው ሳይሳካ ቀርቷል።
ይህንን ውይይት ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ተደርገው ለመጨረሻ ጊዜ የተያዘው ቀጠሮ ለዛሬ ዓርብ ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ነበር። ይሁን እንጂ ቀጠሮው ለጊዜው ባይሳካም፣ አምባሳደሩ በቀጣይ ለመወያየት የሚያደርጉትን ሙከራ እንደማያቋርጡ ተገልጿል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
25/06/2026
ጄኔራል ባጫ ደበሌ የአፍሪካ ህብረት የህወሓትን እርምጃ እንዲያወግዝ ጠየቁ
በቅርቡ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በማፍረስ ወደ ፕሬዝዳንትነት የተመለሱት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ አሳሳቢ የተባለ አዋጅ በመላ ክልሉ ማወጃቸው ይታወሳል። ይህንኑ አዋጅ መመልከታቸውን የገለጹት በናይሮቢ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጄኔራል ባጫ ደበሌ፤ “የክተት አዋጅ እና የግዳጅ ምልመላ” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ ሕዝቡን ለጠቅላላ ጦርነት መቀስቀስ እንደሆነ አመልክተዋል።
ከዚህ ጦርነት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ በስተጀርባ የራስን ጦር እንደገና ማጠናከር እና ታጣቂዎችን እንደ "ቅጥረኛ ተዋጊ" ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን ግጭት መላክ የሚሉ ግቦች እንዳሉ የገለጹት ጄኔራል ባጫ፤ የአፍሪካ ህብረት ይህን የህወሓት ድርጊት በአደባባይ እንዲያወግዝ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ህብረቱ ይህ አዋጅ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመለስና የፖለቲካ ሂደቶች እንዲቀጥሉ ግፊት እንዲያደርግ አምባሳደሩ አሳስበዋል። ሊፈጠር የሚችለውን አላስፈላጊ ቀውስ ለመከላከልም የአፍሪካ ህብረት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
24/06/2026
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ባለሀብት ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ በተለያዩ ሀገራት በበርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ስኬታማ ቢሆኑም፣ በሞሮኮ ያፈሰሱት ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ ግን በአሁኑ ወቅት ከባድ ፈተና ገጥሞታል። በተለይም በሀገሪቱ ብቸኛው የነዳጅ ማጣሪያ የሆነውና የባለሀብቱ ንብረት የሆነው “ሳሚር” (Samir) ኩባንያ፣ ወደ መንግሥት ይዞታነት እንዲዛወር የቀረበው የሕግ ረቂቅ በሞሮኮ ከፍተኛ ምክር ቤት ውድቅ ተደርጓል።
የሞሮኮ የከፍተኛ ምክር ቤት ይህ ኩባንያ በገጠሙት ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት ንብረቱ ተወርሶ ወደ መንግሥት እንዲዛወር የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በትኩረት ከመረመረ በኋላ ውድቅ ማድረጉ ታውቋል። ይህ ውሳኔ በቢሊየነሩ እና በሞሮኮ መንግሥት መካከል ያለውን የከረረ ፍጥጫ ይበልጥ አባባሶታል።
ይህ ግዙፍ የማጣሪያ ፋብሪካ ላለፉት አሥርተ ዓመታት በታየበት የአስተዳደር ጉድለትና አስፈላጊው መዋዕለ ንዋይ ባለመፍሰሱ ምክንያት፣ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ የዕዳ ማጥ ውስጥ ተዘፍቆ ይገኛል። በዚህም ሳቢያ ፋብሪካው ከ2015 ጀምሮ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ተገዷል። በወቅቱ ሼክ አል-አሙዲ በሳዑዲ ዓረቢያ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል በቁም እስር ላይ መቆየታቸው ለኩባንያው አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኙ በማድረግ ለፋብሪካው መዘጋት እንደ አንዱ ምክንያት ይጠቀሳል።
ይሁን እንጂ ሼክ አል-አሙዲ በኩባንያቸው (ኮራል ሞሮኮ ሆልዲንግ) አማካኝነት፣ ለፋብሪካው መዘጋት ተጠያቂው የሞሮኮ መንግሥት ነው የሚል ክስ መስርተዋል። ባለሀብቱ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት (ICSID) በመውሰድ፣ ከሞሮኮ መንግሥት የ2.7 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እየጠየቁ ይገኛሉ። የሞሮኮ መንግሥት በበኩሉ "ውድቀቱ የባለሀብቱ የአስተዳደር ድክመት ውጤት ነው" በሚል በሕግ እየተከራከረ ይገኛል።
በዚህ የሕግ ፍልሚያ መካከል ኩባንያውን ወደ መንግሥት ይዞታነት ለማዛወር የተሞከረው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱ፣ የቢሊየነሩን የንግድ ግዛት ዕጣ ፈንታ ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል። በሞሮኮ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው ይህ ማጣሪያ ፋብሪካ ዳግም ሥራ ይጀምር ወይስ በዕዳው ምክንያት ለሌላ ወገን ይሸጣል? የሚለው ጉዳይ አሁንም በዓለም አቀፍ የዳኝነት ውሳኔ ላይ ተንጠልጥሎ ይገኛል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
22/06/2026
ትውልደ ኢትዮጵያውያን የእስራኤል ወታደሮች በሶማሊላንድ መሰማራታቸው ተገለጸ
እስራኤል ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና መስጠቷን ተከትሎ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ወታደሮቿን በሃርጌሳ ማሰማራቷ ተሰምቷል። እንደ ዘገባው ከሆነ፣ እስራኤል በአሁኑ ወቅት 50 የሚጠጉ ወታደሮችን በሶማሊላንድ ያሰፈረች ሲሆን፣ እነዚህ ወታደሮችም በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው የሁለትዮሽ የጸጥታ ስምምነት መሠረት የተሰማሩ ናቸው።
ወታደራዊ ስምሪቱ በዋናነት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ የእስራኤል ዜጎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ለዚህም እንደ ስልታዊ ምክንያት የቀረበው ወታደሮቹ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ እንዲቀላቀሉ እና የውጭ ኃይል መኖሩን በግልጽ እንዳይታወቅ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ተመልክቷል።
እነዚህ የጦር አባላት በአሁኑ ወቅት በሁለት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተገልጿል፤ እነሱም የሶማሊላንድን ፖሊስ እና የጦር ኃይል የማሰልጠን ስራ እንዲሁም በእስራኤልና ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመውን የጸጥታ ስምምነት የማስፈጸም ስራ ናቸው።
እስራኤል ሶማሊላንድን በይፋ እውቅና ከሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗ የሚታወስ ሲሆን፣ በቀጣይም በሶማሊላንድ ያላትን የወታደራዊ አባላት ቁጥር የመጨመር እና ስልታዊ ጠቀሜታ ያለው ወታደራዊ ጣቢያ የመገንባት ፍላጎት እንዳላት ተጠቁሟል። ይህ እንቅስቃሴ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ካደረገችው የመግባቢያ ስምምነት (MoU) በኋላ በቀጣናው እየታዩ ካሉ ጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጦች ጋር ተያይዞ ትኩረትን ስቧል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
22/06/2026
በአፋር ክልል የህወሓት ኃይሎች የከባድ መሣሪያ ጥቃት ፈጸሙ።
የሞርተር ጥቃቱ የተፈጸመው በአፋር ክልል ዞን 2 በመጋሌ ወረዳ አራዱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የአፋር ክልል አድማ ብተና ኃይል የሰፈረበትን ካምፕ መሆኑን ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን፣ ከጥቃቱ በኋላ የተሰጠ አጸፋዊ ምላሽ እስካሁን የለም። በጥቃቱም ስለደረሰው ጉዳትም ሆነ ስለጠፋው የሰው ሕይወት የተገለጸ መረጃ የለም።
ይህ የሞርተር ጥቃት በቅርቡ የፌደራል መንግሥቱ እየወሰደ ያለውን ተከታታይ የአየርና የድሮን ጥቃቶች ተከትሎ በህወሓት በኩል እንደ አጸፋዊ ምላሽ የተወሰደ ሊሆን ይችላል የሚሉ ግምቶች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ህወሓት ወይም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአፋር ክልል መንግሥት ላይ 'በመሬት ላይ ለጸረ-ህወሓት ኃይሎች ድጋፍ እየሰጣችሁ ነው፣ በትግራይ ክልል ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙም አመቻችታችኋል' የሚሉ ክሶችን ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል። እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ከአፋር ክልል መንግሥትም ሆነ ከህወሓት በኩል የተሰጠ መረጃ የለም።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
19/06/2026
የትግራይ ኃይሎች በወልቃይት ትንኮሳ ሲፈጽሙ፣ የአየር ጥቃትም መፈጸሙ ታውቋል።
ዛሬ አርብ ሰኔ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በሱዳን በኩል የተነሱ ‘አርሚ 70’ ተብሎ የሚጠራው የህወሓት ጦር አባላት፣ ማለዳ አካባቢ ሱዳን እና ኢትዮጵያን በሚያዋስነው የሸረሪና መስመር በኩል ትንኮሳ ፈጽመው እንደነበር የታወቀ ሲሆን፤ ጥቂት ሰዓታት ከፈጀ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ጥቃቱን የሰነዘረው ኃይል ወደ ኋላ መመለሱ ተነግሯል።
ከትንኮሳው በኋላም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል። ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት ዝርዝር መረጃ ባይገኝም፣ በድንበር አካባቢ በሚገኝ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ የአሜሪካን እርምጃ በመቃወም በግላቸው መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እየሞቱ በጥቂት ግለሰቦች የቪዛ እገዳ ላይ ማተኮር ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን አይገባም” ብለዋል። በተመሳሳይ አመሻሽ ላይም ህወሓት የአሜሪካን ማዕቀብ በማውገዝ መግለጫ ሰጥቷል።"
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia
19/06/2026
ዶ/ር ደብረጽዮንም ሆኑ ምክትላቸው በአሜሪካ የቪዛ እገዳ ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከአንድ ቀን በፊት “ጽንፈኛ” ሲል በጠራቸው የህወሃት አመራሮች ላይ የቪዛ እገዳ መጣሉን ማሳወቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ መሥሪያ ቤቱ ሰላም እንዲደፈረስ እያደረጉ ነው ባላቸው አመራሮች ላይ እገዳው መጣሉን ቢገልጽም፣ ስማቸውን ግን በይፋ አልጠቀሰም ነበር። አሁን ዘግይተው ከዲፕሎማሲያዊ ምንጮች በደረሱን መረጃዎች መሰረት፣ በአሁኑ ወቅት ክልሉን እያስተዳደሩ የሚገኙት የህወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው እንዳልተካተተ ተመላክቷል።
እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ እገዳው ያረፈባቸው ስድስት ግለሰቦች ሲሆኑ ዝርዝሩ ሁለት የፖለቲካ አመራሮችን እና አራት ወታደራዊ አዛዦችን ያካተተ ነው። በዚህም መሰረት የህወሃት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር እና የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል። ወታደራዊ መኮንኖቹን በተመለከተም ጄነራል ምግበ ኃይሌ፣ ጄነራል ኃይለሥላሴ ግርማይ (ወዲ እምበይተይ)፣ ጄነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ (ጆን መዲድ) እና ጄነራል አብርሃ ተስፋይ (ድንኩል) የእገዳው ሰለባ መሆናቸው ታውቋል። በተጨማሪም ከቡድኑ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው አንድ ነጋዴ በልዩ ሁኔታ በዝርዝሩ ውስጥ መካተታቸው ተመልክቷል።
የአሜሪካ መንግስት ይፋዊ መግለጫውን ካወጣ በኋላ በስም የጠቀሰው አካል ባይኖርም፣ አሁን ላይ ትግራይን እያስተዳደሩ የሚገኙት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልም ሆኑ ከእርሳቸው በፊት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር የነበሩት ጄነራል ታደሰ ወረደ በስም ዝርዝሩ ውስጥ አልተካተቱም። በተመሳሳይ አሁን ላይ በክልሉ ምክትል ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አቶ አማኑኤል አሰፋም በዚሁ የእገዳ ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተቱ ለማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ የቪዛ እገዳ የተጣለው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ወደ መቀሌ ተጉዘው ከዶክተር ደብረጽዮን እና ከሌሎች አመራሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ መሆኑ ይታወሳል። በቀጣይ ቀናትም በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር እርቪን ማሲንጋ ወደ መቀሌ አቅንተው፣ ግጭቱ ዳግም እንዳያገረሽ ከክልሉ አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸው ተነግሯል።
የበለጠ መረጃ t.me/times_mereja_ethiopia